በኦሮሚያ ክልል 6700 ሰዎች ሃሰተኛ ሠነዶች ይዘው ተገኙ

ሀሰተኛ ሰነድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቁጥራቸው 6700 የሚሆን የኦሮሚያ ክልል የህዝብ ሰራተኞች የመንጃ ፈቃዶች እና የብቃት መማረጋገጫ ሰርቲፊኬትን (ሲኦሲ) ጨምሮ ሃሰተኛ የስራ እና የትምህርት ሠነዶችን ይዘው ተገኝተዋል። የኦሮሚያ ክልል የፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሀይል ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሰራተኞቹ የአመራር ስፍራን ጨምሮ በተለያዩ መደቦች ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው ብለዋል።

እንደ ሀላፊው ገለፃ ግማሽ ሚሊዮን ከሚሆነው የመንግስት ስራ ላይ የተሰማራ ሰው አንፃር አሃዙ አነስተኛ ነው ብለዋል። ነገር ግን በጥቆማ ሰጪዎችና በመርማሪዎች እገዛ በሃሰተኛ ሠነዶች የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ቁጥር መጋለጥ ሊጨምር እንደሚችል አሳውቀዋል።

ዶ/ር ቢቂላ አክለውም ከጊዜ ጊዜ እያደገ የመጣው የሃሰተኛ ሠነዶች ጉዳይ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ብልሹነት ቢሮውን ለምርመራ እንዳነሳሳው ይናገራሉ።

ቢሮው እጃቸው ላይ ሃሰተኛ ሠነዶች ይዘው የሚገኙ ሰዎች ከሐምሌ 15 እስከ ነሐሴ 22 2009 ዓ.ም. ባለው ጊዜ በራሳቸው ፈቃድ እራሳቸውን እንዲያጋልጡ የእፎይታ ጊዜ ሰጥቶ እንደነበር ሃላፊው አስታውሰዋል። ይህንን ተከትሎም ሃሰተኛ ሠነዶች እንዳላቸው ያሳወቁ ግለሰቦች ባላቸው እውነተኛ ሠነዶች መሠረት እንደሚመደቡ ሃላፊው አስታውቀዋል።

ነገር ግን በተሰጣቸው ጊዜ ሃሰተኛ ሠነዶችን ማስረከብ ያልቻሉ ሰዎች ምርመራ ተደርጎባቸው ህግ ፊት እንዲቀርቡ ይደረጋል። ባልተገባ መንገድም ሲቀበሉ የነበረውን ደሞዝ እና ጥቅማጥቅምም እንዲመልሱ እንደሚደረግ ዶ/ር ቢቂላ አስረግጠዋል።

ሃሰተኛ ሠነዶች ይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የእምነት ክህደት ቃልን ከመሰብሰብ ጀምሮ ማሕበረሰቡ በ888 ነፃ የስልክ መስመር የሚያደርገው ጥቆማ እንደ መረጃ እንደሚቀርብባቸው እና ምርመራው እስከ መጪው መስከረም 22. 2010 ዓ.ም. ድረስ እንደሚቀጥል ሃላፊው ገልፀዋል።

ቢሮው አዲስ የተቀላቀሉ የመንግስት ሰራተኞችም ላይ የሰነድ ማጣራት ምርመራ ወደፊት እንደሚካሄድባቸው አስታውቋል።

ከጥቂት ወራት በፊት የጋምቤላ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የክልሉን ዘጠኝ ከፍተኛ አመራሮች ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል በሚል ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጋቸው ይታወሳል። በተመሳሳይም የደቡብ ክልል የስነ ምግባርና የፀረ ሙሰና ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜ መንግስታዊ ሰነዶችን አስመስሎ በማዘጋጀትና በመጠቀም ወንጀል በርካታ ግለሰቦች ላይ ክስ መስርቷል።

ባለፈው ግንቦት ወርም የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በተቋሙ ሲሰሩ የነበሩ 20 የአስተዳደር ዘርፍ ሠራተኞችን ከሥራ አሰናብቷል። የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለፉት ዓመታት ውስጥ በርካታ ግለሰቦችን የሃሰት ማስረጃ አቅርባችኋል በሚል ክስ መመስረቱ ከድረ-ገጹ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።